11 ነዶው ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዘው፤ ካህኑ ነዶውን የሚወዘውዘው በሰንበት ቀን ማግስት ነው።
12 ነዶውን በምትወዘውዙበት ቀን እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ፤
13 ከዚህም ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ለእህል ቊርባን፣ አንድ አራተኛ የኢን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቊርባን አቅርቡ።
14 ስጦታውን ለአምላካችሁ (ኤሎሂም) እስከምታቀርቡበት እስከዚያ ቀን ድረስ እንጀራም ቢሆን፣ ቈሎ ወይም እሸት አትብሉ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።
15 “ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቊጠሩ።
16 እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቊጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።
17 በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አምጡ።