ዘሌዋውያን 24:3-9 NASV

3 አሮንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ መጋረጃ ውጭ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያሉትን መብራቶች ከምሽት እስከ ንጋት ያለ ማቋረጥ ያሰናዳቸው፤ ይህም ለትውል ዶቻችሁ ሥርዐት ነው።

4 በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ ያሉት መብራቶች ያለ ማቋረጥ መሰናዳት አለባቸው።

5 “የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ እያንዳንዱ ኅብስትም በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ይጋገር።

6 እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ረድፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ባለው የንጹሕ ወርቅ ጠረጴዛ ላይ አኑራቸው።

7 ከኅብስቱ ጋር የመታሰቢያ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት እንዲሆን ንጹሕ ዕጣን በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ አኑር።

8 ኅብስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ይወክል ዘንድ ዘወትር በየሰንበቱ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይደርደር፤ ይህም የዘላለም ቃል ኪዳን ነው።

9 ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።”