2 “ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴን አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
3 “ ‘በሥርዐቴ ብትሄዱ፤ ትእዛዜንም በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣
4 ዝናብን በወቅቱ እሰጣችኋለሁ፤ ምድሪቱ እህልዋን፣ የሜዳ ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ።
5 የምትወቁት እህል፣ የወይን ዘለላ እስከምትቈርጡበት ጊዜ፣ የምትቈርጡትም የወይን ዘለላ፣ እህል እስከምትዘሩበት ጊዜ ያደርሷችኋል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
6 “ ‘በምድሪቱ ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ ማንም አያስፈራችሁም። ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም።
7 ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነርሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
8 ከእናንተ አምስቱ መቶውን፣ መቶውም ዐሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።