ዘሌዋውያን

ምዕራፎች 26:41-46

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

41ይኸውም፣ እኔ ጠላት እንድሆንባቸውና ወደ ጠላቶቻቸው ምድር እንድሰዳቸው ያደረገኝን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድና ስለ ኀጢአታቸው የሚገባውን ቅጣት ቢቀበሉ፣ 42በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይስሐቅም ጋር የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባታለሁ። 43ምድሪቱ እነርሱ ለቀዋት ስለ ሄዱ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱ በሌሉበት ጊዜም ባድማ ሆና በሰንበትዋ ትደሰታለች፤ ሕጌን በማቃለላቸውና ሥርዐቴን በመናቃቸው፣ የኀጢአታቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። 44በዚህ ሁሉ ግን ከእነርሱ ጋር የገባሁትን ኪዳኔን በማፍረስ፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ፈጽሜ እስካጠፋቸው ድረስ አልተዋቸውም፤ አልጸየፋቸውምም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ። 45ስለ እነርሱም ስል፣ አምላካቸው (ኤሎሂም) እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ” 46 እግዚአብሔር (ያህዌ) በራሱና በእስራኤላውያን መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ በኩል ያቆማቸው ሥርዐቶች፣ ሕጎችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።