20 ዕርሻውን ባይዋጅ ወይም ለሌላ ሰው አሳልፎ ቢሸጥ፣ ከዚያ በኋላ ሊዋጀው አይችልም።
21 እርሻው በኢዮቤልዩ በሚለቀ ቅበት ጊዜ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንደተሰጠ ዕርሻ ተቈጥሮ ቅዱስና የካህናቱ ንብረት ይሆናል።
22 “ ‘አንድ ሰው የወረሰው ርስት ያልሆነውን፣ በገንዘቡ የገዛውን የዕርሻ መሬት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ቢቀድስ፣
23 ካህኑ የእርሻውን መሬት ዋጋ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ መጠን ይተምናል፤ ሰውየው የተተመነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ አድርጎ በዚያኑ ዕለት ይክፈል።
24 በኢዮቤልዩ ዓመትም የዕርሻው መሬት የቀድሞው ባለ ርስት ለነበረው፣ ለሸጠውም ሰው ይመለሳል።
25 እያንዳንዱ ዋጋ የሚተመነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ ሆኖ አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው።
26 “ ‘የእንስሳት በኵር ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ ሆነ፣ ማንም ሰው የእንስሳትን በኵር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አይችልም፤ በሬም ሆነ በግ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ነውና።