ዘኁልቍ 11:13-19 NASV

13 ለዚህ ሁሉ ሕዝብስ ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? ሁሉም ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን’ እያሉ ያለቅሱብኛል።

14 እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም።

15 እንዲህስ ከምታደርገኝ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።”

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋር ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ።

17 ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል።

18 “ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብፅ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰምቶአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ።

19 የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለአምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤