ዘኁልቍ 11:28-34 NASV

28 ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ።

29 ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ተቈርቍረህ ነውን? የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም (ያህዌ) መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤

30 ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ።

31 በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣ ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው፤

32 በዚያን ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግሥቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት።

33 ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ።

34 ሌላ ምግብ ለማግኘት የጐመጁትን ሰዎች በዚያ ስለ ቀበሩአቸው የቦታው ስም “ቂብሮት ሃታአባ” ተባለ።