ዘኁልቍ 16:36-42 NASV

36 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

37 “ጥናዎቹ የተቀደሱ ናቸውና ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ ወስደህ በውስጣቸው ያለውን ፍም አርቆ እንዲደፋ ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር ንገረው፤

38 እነዚህም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ኀጢአት የሠሩ ሰዎች ጥና ናቸው፤ ጥናዎቹም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የቀረቡና የተቀደሱ በመሆናቸው ለመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጥቅጠህ አሣሣቸው፤ እነዚህም ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ይሁኑ።”

39 ከዚህ የተነሣም ካህኑ አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች አምጥተዋቸው የነበሩትን የናስ ጥናዎች ሰብስቦ የመሠዊያው መለበጫ እንዲሆኑ ቀጠቀጣቸው፤

40 ይህን ያደረገውም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት ነው፤ ይህም ከአሮን ዘር በስተቀር ማንም ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቀርቦ ዕጣን እንዳያጥን ያለበለዚያ ግን፣ እንደ ቆሬና እንደ ተከታዮቹ እንደሚሆን ለእስራኤላውያን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነበር።

41 በማግሥቱም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ፣ “እናንተ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ።

42 ማኅበሩም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን ዘወር ሲሉ ደመና ድንኳኑን በድንገት ሸፍኖት አዩ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ተገለጠ።