ዘኁልቍ 18:1-6 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “መቅደሱን በተመለከተ ስለሚፈጸም በደል አንተ፣ ልጆችህና የአባትህ ቤተ ሰቦች ኀላፊነቱን ትሸከማላችሁ፤ ክህነቱን በተመለከተ ስለሚፈጸም በደል ግን ኀላፊነቱ የሚወድቀው በአንተና በልጆችህ ላይ ብቻ ነው።

2 አንተና ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት በምታገለግሉበት ጊዜ አብረዋችሁ እንዲሆኑና እንዲረዱአችሁ ከአባትህ ነገድ ሌዋውያንን አምጣቸው።

3 እነርሱም በአንተ ኀላፊነት ሥር ሆነው የድንኳኑን አገልግሎት በሙሉ ያከናውኑ፤ ይሁን እንጂ ወደ መቅደሱ ዕቃዎችም ሆነ ወደ መሠዊያው አይጠጉ፤ ከተጠጉ ግን እነርሱም አንተም ትሞታላችሁ።

4 እነርሱም የመገናኛውን ድንኳን ለመንከባከብ ማለትም በድንኳኑ ውስጥ የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ኀላፊነት በመውሰድ አብረዋችሁ ይሁኑ፤ ከዚህ በተረፈ ግን እናንተ ወዳላችሁበት ማንም ሰው አይጠጋ።

5 “በእስራኤላውያን ላይ ዳግም ቊጣ እንዳይደርስባቸው የመቅደሱና የመሠዊያው እንክብካቤ ኀላፊነት የሚመለከተው እናንተን ይሆናል።

6 ከእስራኤላውያን መካከል ወገኖቻችሁን ሌዋውያንን ለእናንተ ስጦታ አድርጌ እኔ ራሴ መርጫቸዋለሁ፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ ሁሉ እንዲሠሩ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጡ ናቸው።