ዘኁልቍ 18:14-20 NASV

14 “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ የተሰጠ በእስራኤል ያለ ማንኛውም ነገር ሁሉ የአንተ ነው።

15 ማሕፀን የሚከፍትና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ ሰውም ሆነ እንሰሳ የአንተ ነው፤ ነገር ግን ማንኛውም በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅና ንጹሕ ካልሆነ እንስሳ በኵር ሆኖ የተወለደውን ተባዕት ሁሉ ዋጀው።

16 እነዚህም አንድ ወር ሲሆናቸው ሃያ ጌራ በሚመዝነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ፣ በተወሰነው በመዋጃው ዋጋ በአምስት ሰቅል ጥሬ ብር ትዋጀዋለህ።

17 “የተቀደሱ ስለሆኑ የበሬ፣ የበግ ወይም የፍየል በኵር የሆኑትን አትዋጃቸውም፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፤ ሥባቸውንም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ ታቃጥለዋለህ።

18 የሚወዘወዘው ቊርባን ፍርምባና የቀኙ ወርች የአንተ እንደሆነ ሁሉ የእነዚህም ሥጋ የአንተ ይሆናል።

19 እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚያቀርቡት ከተቀደሰ ቊርባን የሚለየው ሁሉ ለአንተ፣ ለወንድና ለሴት ልጆችህ መደበኛ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለአንተና ለዘሮችህ ዘላለማዊ የጨው ኪዳን ነው።”

20 እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን እንዲህ አለው፤ “ከምድራቸው የምትካፈለው ርስት፣ ከእነርሱም የምታገኘው ድርሻ የለህም፤ በእስራኤላውያን መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ።