ዘኁልቍ 19:14-20 NASV

14 “አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዐት የሚከተለው ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ በዚያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል፤

15 እንዲሁም ያልተከደነ ማንኛውም ክፍት ዕቃ የረከሰ ይሆናል።

16 “ሜዳ ላይ በሰይፍ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ወይም ደግሞ ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል።

17 “ለረከሰውም ሰው፣ ለማንጻት ከተቃጠለው የጊደር ዐመድ ላይ ማሰሮ ውስጥ በማድረግ በላዩ የምንጭ ውሃ ይጨምሩበት።

18 ከዚያም በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ሰው ሂሶጵ ወስዶ በውሃው ውስጥ ከነከረው በኋላ ድንኳኑን፣ በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ፣ እዚያ የነበሩትንም ሰዎች ሁሉ ይርጫቸው። እንዲሁም የሰው ዐፅም ወይም መቃብር ወይም ደግሞ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ሰው የነካው ማንኛውንም ሰው ይርጭ።

19 የነጻው ሰው ያልነጻውን ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ይርጨው፤ በሰባተኛው ቀን ያንጻው፤ የሚነጻውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ ማምሻውም ላይ የነጻ ይሆናል።

20 ይሁን እንጂ አንድ የረከሰ ሰው ራሱን ሳያነጻ ከቀረ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መቅደስ አርክሶአልና ከማኅበረ ሰቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ የሚያነጻው ውሃ ያልተረጨበት ስለ ሆነ ርኩስ ነው።