3 ሙሴን ተጣሉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሞቱ ጊዜ ምነው እኛም ያኔ ሞተን ባረፍነው ኖሮ!
4 የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማኅበረሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድ ነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን?
5 ከግብፅ አውጥታችሁ እህል ወይም በለስ፣ ወይን ወይም ሮማን ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ቦታ ያመጣችሁንስ ለምንድ ነው? የሚጠጣ ውሃ እንኳ ይታጣ!”
6 ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር ተገለጠላቸው።
7 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
8 “በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብሰቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።”
9 ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወሰደ።