ዘኁልቍ 21:1-6 NASV

1 በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ እስራኤል በአታሪም መንገድ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ።

2 በዚያን ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን” ሲል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ተሳለ።

3 እግዚአብሔርም (ያህዌ) የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ ተባለ።

4 እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግሥቱ አለቀ፤

5 በእግዚአብሔርና (ኤሎሂም) በሙሴም ላይ ተነሥተው፣ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድ ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” ሲሉ ተናገሩ።

6 በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መርዘኛ እባቦች ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ።