ዘኁልቍ 22:28-34 NASV

28 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የአህያዪቱን አፍ ከፈተ፤ በለዓምንም፣ “እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌህ ነው?” አለችው።

29 በለዓምም መልሶ አህያዪቱን፣ “ስላላገጥሽብኝ ነዋ! በእጄ ሰይፍ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁኑኑ በገደልሁሽ ነበር” አላት።

30 አህያዪቱም ደግሞ በለዓምን እንዲህ አለችው፣ “ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተቀመጥክብኝ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ይህን የመሰለ ነገር የማድረግ ልማድ ነበረኝ?”እርሱም፣ “በጭራሽ!” አላት።

31 በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የበለዓምን ዐይን ከፈተ፤ እርሱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ እንደ ያዘ መንገዱ ላይ ቆሞ አየ፤ ጐንበስ ብሎም በግንባሩ ተደፋ።

32 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ስለ ምንድ ነው? መንገድህ በፊቴ ጠማማ ስለ ሆነ ልቃወምህ መጥቻለሁ።

33 አህያዪቱ አይታኝ ሦስቱንም ጊዜ ከፊቴ ዞር ባትልማ ኖሮ በእውነት እስካሁን አንተን በገደልሁህ አህያዪቱን ግን በሕይወት በተውኳት ነበር።

34 በለዓምም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መልአክ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ እኔን ለመቃወም መንገዱ ላይ መቆምህን አላወቅሁም፤ አሁንም ደስ የማትሰኝ ከሆነ እመለሳለሁ” አለው።