ዘኁልቍ 23:10-16 NASV

10 የያዕቆብን ትቢያ ማን ቈጥሮ ይዘልቃል?የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቈጥረዋል።የጻድቁን ሞት እኔ ልሙት፤ፍጻሜዬም የእርሱ ዐይነት ፍጻሜ ትሁን!”

11 ባላቅም በለዓምን፣ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ አመጣሁህ፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አላደረግህልኝም!” አለው።

12 እርሱም መልሶ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በአፌ ያስቀመጠውን መናገር አይገባኝምን?” አለው።

13 ከዚህ በኋላ ባላቅ፣ “እነርሱን ማየት ወደ ምትችልበት ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ እዚያም ሁሉን ሳይሆን በከፊል ብቻ ታያቸዋለህ፤ እዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው።

14 ስለዚህም በፈስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወዳለው ወደ ጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያ ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።

15 በለዓምም ባላቅን፣ “እርሱን ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ” አለው።

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) በለዓምን ተገናኘው፤ በአፉም መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና ይህን መልእክት ንገረው” አለው።