ዘኁልቍ 23:8-14 NASV

8 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ያልረገመውን፣እኔ እንዴት ረግማለሁ? እግዚአብሔር (ያህዌ) ያላወገዘውንስ፣እንዴት አወግዛለሁ?

9 ከዐለታማ ተራሮች ጫፍ ሆኜ አየዋለሁ፤በከፍታዎቹም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ተለይቶ የሚኖረውን፣ራሱንም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የማይቈጥረውን፣ ሕዝብ አያለሁ።

10 የያዕቆብን ትቢያ ማን ቈጥሮ ይዘልቃል?የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቈጥረዋል።የጻድቁን ሞት እኔ ልሙት፤ፍጻሜዬም የእርሱ ዐይነት ፍጻሜ ትሁን!”

11 ባላቅም በለዓምን፣ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ አመጣሁህ፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አላደረግህልኝም!” አለው።

12 እርሱም መልሶ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በአፌ ያስቀመጠውን መናገር አይገባኝምን?” አለው።

13 ከዚህ በኋላ ባላቅ፣ “እነርሱን ማየት ወደ ምትችልበት ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ እዚያም ሁሉን ሳይሆን በከፊል ብቻ ታያቸዋለህ፤ እዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው።

14 ስለዚህም በፈስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወዳለው ወደ ጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያ ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።