ዘኁልቍ 28:11-17 NASV

11 “ ‘በየወሩ መባቻ እንከን የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።

12 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤

13 እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

14 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን የኢን ግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢን አንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

15 ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይቀርባል።

16 “ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይከበራል።

17 በዚሁ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብሉ።