ዘኁልቍ 28:13-19 NASV

13 እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

14 ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን የኢን ግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢን አንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

15 ከመጠጥ ቊርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይቀርባል።

16 “ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይከበራል።

17 በዚሁ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብሉ።

18 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አትሥሩበት።

19 እንከን የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ።