1 “ ‘በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ሥራም አትሥሩበት፤ ይህም የመለከት ድምፅ የምታሰሙበት ቀናችሁ ነው።
2 እንከን የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።
3 ከወይፈኑ ጋር ለእህል ቊርባን የሚሆን የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራውም በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ፣ በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት አቅርቡ፤
4 ከእያንዳንዱም ሰባት የበግ ጠቦት ጋር በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ።
5 ማስተስረያ እንዲሆናችሁም አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ በተጨማሪ አቅርቡ።
6 እነዚህ እንግዲህ በተደነገገው መሠረት ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋር በየዕለቱና በየወሩ ከሚቀርቡት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ሌላ ተጨማሪ ሆነው፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሽታቸው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርቡ መሥዋዕቶች ናቸው።