17 ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ ታጥቀንና በእስራኤላውያን ፊት ግንባር ቀደም ሆነን ለመሄድ ዝግጁ ነን፤ በዚህም ጊዜ ሴቶቻችንና ልጆቻችን በምድሪቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች እንዲጠበቁ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ።
18 እኛም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ርስቱን እስኪወርስ ድረስ ወደየቤታችን አንመለስም።
19 ድርሻችንን ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ስላገኘን፣ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእነርሱ ጋር የምንካፈለው አንዳችም ርስት አይኖርም።”
20 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ብታደርጉ ማለትም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ታጥቃችሁ ለጦርነት ብትዘጋጁ፣
21 እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ አሳዶ እስኪያስወጣ ድረስ ሁላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዝግጁ ሆናችሁ ዮርዳኖስን ብትሻገሩ፣
22 ምድሪቱ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከተገዛች በኋላ ልትመለሱ ትችላላችሁ፤ ለእግዚአብሔርና (ያህዌ) ለእስራኤል ካለባችሁም ግዴታ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህችም ምድር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ርስታችሁ ትሆናለች።
23 “ይህን ባታደርጉ ግን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ትበድላላችሁ፤ ኀጢአታችሁ እንደሚያገኛችሁም ዕወቁ።