ዘኁልቍ 33:49-55 NASV

49 እዚያም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ከቤት የሺሞት እስከ አቤልስጢም ባለው ስፍራ ሰፈሩ።

50 ከኢያሪኮ ማዶ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው በሞዓብ ሜዳ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

51 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን ስትሻገሩ፣

52 የምድሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ከፊታችሁ አሳዳችሁ አስወጧቸው፤ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶቻቸውን በሙሉ አጥፉ፤ እንዲሁም በኰረብታ ላይ የተሠሩትን መስገጃዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ።

53 ምድሪቱን ርስት አድርጌ ሰጥቻችኋለሁና ውረሷት፤ ኑሩባትም።

54 ምድሪቱንም በየጐሣዎቻችሁ በዕጣ ተከፋፈሉ። ከፍ ያለ ቊጥር ላለው ሰፋ ያለውን፣ ዝቅተኛ ቊጥር ላለው ደግሞ አነስተኛውን ስጡ፤ ምንም ይሁን ምን በዕጣ የወጣላቸው፣ የየራሳቸው ርስት ይሆናል። አከፋፈሉም በየአባቶቻችሁ ነገዶች አንጻር ይሁን።

55 “ ‘የምድሪቱን ነዋሪዎች አሳዳችሁ ሳታስወጧቸው ብትቀሩ ግን፣ እንዲኖሩ የተዋችኋቸው ሰዎች ለዐይናችሁ ስንጥር፣ ለጐናችሁም እሾኽ ይሆኑባችኋል፤ በምትኖሩበትም ምድር ችግር ይፈጥሩባችኋል።