ዘኁልቍ 6:18-24 NASV

18 “ ‘ከዚያም ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጒር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጨው፤ ጠጒሩንም ወስዶ ከኅብረቱ መሥዋዕት ሥር በሚነደው እሳት ውስጥ ይጨምረው።

19 “ ‘ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጒር ከተላጨ በኋላ፣ ካህኑ የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች እንዲሁም ከመሶቡ ላይ እርሾ የሌለበትን አንድ ወፍራምና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊው ያስይዘው

20 ከዚያም ካህኑ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም የተቀደሱ ናቸው። ከተወዘወዘው ፍርምባና ከቀረበው ወርች ጋር የተቀደሱ የካህኑ ድርሻ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል።

21 “ ‘ስእለቱን ለመፈጸም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለሚሳል ናዝራዊ ሕጉ ይኸው ነው፤ ሊቀርብ ከሚችለው በላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለመስጠት ቃል ለሚገባው ነገር እንደ ናዝራዊነቱ በተሳለው መሠረት መሆን አለበት። በናዝራዊነት ሕግ መሠረት የተሳለውን ስእለት መፈጸም ይገባዋል።’ ”

22 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

23 “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ‘እስራኤላውያንን በምትባርኩበት ጊዜ እንዲህ በሉአቸው፤

24 “ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ይባርክህ፤ይጠብቅህም፤