ዘፀአት 1:14-20 NASV

14 ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በእርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብፃውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።

15 የግብፅም ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን ሴቶች አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤

16 “የዕብራውያንን ሴቶች በማማጫው ድንጋይ ላይ በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።”

17 አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለ ፈሩ የግብፅ ንጉሥ ያዘዛቸውን አልፈጸሙም፤ ወንዶቹንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው።

18 ንጉሡም አዋላጆቹን ጠርቶ፣ “ለምንድን ነው ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው?” አላቸው።

19 እነርሱም፣ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፃውያን ሴቶች አይደሉም፤ ብርቱዎች ስለሆኑ አዋላጆች ከመድረሳቸው በፊት ይወልዳሉ” ሲሉ ለፈርዖን መለሱለት።

20 ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለአዋላጆቹ መልካም ሆነላቸው፤ ሕዝቡም በቍጥር እየበዛና እያየለ ሄደ።