ዘፀአት 10:4-10 NASV

4 እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ።

5 አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል።

6 የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብፃውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።

7 የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብፅ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን? አሉት።

8 ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ።

9 ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።

10 ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋር እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር ይሁን ነገር ግን ተንኰል አስባችኋል።