ዘፀአት 11:1-7 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ሌላ መቅሠፍት አወርድባቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፈርዖን ይለቃችኋል፤ ሲለቃችሁም አንዳችሁን ሳያስቀር ያስወጣችኋል።

2 ለእስራኤል ሕዝብ ለወንዶቹም ሆነ ለሴቶቹ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ከየጐረቤቶቻቸው ስጡን ብለው እንዲወስዱ ንገራቸው።

3 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እስራኤላውያን በግብፃውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብፅ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ።

4 ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ።

5 በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያይቱ ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል።

6 በግብፅ ምድር ሁሉ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ወደ ፊትም የማይሰማ ታላቅ ዋይታ ይሆናል።

7 በእስራኤላውያን ዘንድ ግን በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም።’ በዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የሚያደርግ መሆኑን ታውቃላችሁ።