ዘፀአት 11:3-9 NASV

3 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እስራኤላውያን በግብፃውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብፅ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ።

4 ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ።

5 በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያይቱ ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል።

6 በግብፅ ምድር ሁሉ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ወደ ፊትም የማይሰማ ታላቅ ዋይታ ይሆናል።

7 በእስራኤላውያን ዘንድ ግን በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም።’ በዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የሚያደርግ መሆኑን ታውቃላችሁ።

8 ሹማምትህ በሙሉ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እጅ እየነሡም ‘አንተም ሆንህ የምትመራቸው ሰዎች በሙሉ ውጡልን’ ብለው ይለምኑኛል፤ እኔም ከዚያ በኋላ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሙሴ በታላቅ ቍጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።

9 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን “ድንቅ ሥራዎቼ በግብፅ ምድር በብዛት ይታዩ ዘንድ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው።