ዘፀአት 31:13-18 NASV

13 “ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደሆንሁ እንድታውቁ ነው።

14 “ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢሽረው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ።

15 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት።

16 እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤

17 በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፎአልና።’ ”

18 እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ መናገሩን ከፈጸመ በኋላ፣ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች፣ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ለእርሱ ሰጠው።