3 ማርና ወተት ወደምታፈሰው ምድር ውጡ፤ ነገር ግን አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆናችሁ፣ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሄድም።”
4 ሕዝቡም እነዚህን አሳዛኝ ቃላት በሰሙ ጊዜ ይተክዙ ጀመር፤ ማንም ሰው አንዳች ጌጥ አላደረገም።
5 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን፣ “እስራኤላውያንን፣ ‘እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ለአንዳፍታ እንኳ ከእናንተ ጋር አብሬአችሁ ብሄድ አጠፋችሁ ነበር፤ አሁንም ጌጣጌጦቻችሁን አውልቁ፤ እናንተን ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ ብለህ ንገራቸው” አለው።
6 ስለዚህ እስራኤላውያን በኮሬብ ተራራ ላይ ጌጣጌጦቻቸውን አወለቁ።
7 ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን (ያህዌ) መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር።
8 ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቁመው ይጠባበቁ ነበር።
9 ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሙሴ ጋር እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር።