ሉቃስ 11:26-32 NASV

26 ከዚያም በኋላ ሄዶ ሌሎች ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያ ሰው ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆንበታል።

27 ኢየሱስ ይህን እየተናገረ እያለ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” አለችው።

28 እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ።

29 ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ በሄደ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ታምራዊ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ አይሰጠውም።

30 ምክንያቱም ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደሆናቸው የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል።

31 የደቡቧ ንግሥት በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ እርሷ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።

32 የነነዌ ሰዎችም በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።