ሉቃስ 20:15-21 NASV

15 ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል?

16 መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።”ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ።

17 ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጒሙ ምንድን ነው?

18 በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቃል።”

19 ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህንን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያኑ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።

20 ኢየሱስን አሳልፈው ለገዥው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት።

21 ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደ ምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን።