4 ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤“በበረሓ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ጐዳናውንም አቅኑ፤
5 ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ጠማማው መንገድ ቀና፣ሸካራውም ጐዳና ትክክል ይሆናል፤
6 የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ”
7 ዮሐንስም በእርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ ይላቸው ነበር፤ “እናንት የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ?
8 እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባታችን አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና።
9 አሁን እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራም ዛፍ ሁሉ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል።”
10 ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።