33 ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይ በላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤
34 የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፣ ‘በላተኛና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና “የኀጢአተኞች” ወዳጅ’ አላችሁት።
35 እንግዲህ የጥበብ ትክክለኛነት በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”
36 ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ።
37 በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቶ ይዛ መጣች፤
38 ከበስተ ኋላው እግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሩን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጒር ታብሰው ጀመር፤ እግሩንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው።
39 የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ አሰበ።