ሉቃስ
ምዕራፎች 8:30-36
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
30ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው።
31አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዛቸውም አጥብቀው ለመኑት።
32በዚያም አካባቢ በተራራ ወገብ ላይ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሣማው መንጋ ግቡ ብሎ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው።
33አጋንንቱም ከሰውየው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ የዐሣማውም መንጋ በገደሉ አፋፍ ቊልቊል በመንደርደር ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ።
34እረኞቹም የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ፣ ሸሽተው በመሄድ በከተማውና በገጠሩ አወሩ።
35ሕዝቡም የተደረገውን ነገር ለማየት ከያሉበት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶ፣ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በኢየሱስም እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ።
36በአጋንንት የተያዘው ሰው ሲድን ያዩትም፣ እንዴት እንደ ዳነ ለሕዝቡ አወሩላቸው።