12 ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “ከእናንተ ማንም ደም አይብላ፤ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛም ቢሆን ደም አይብላ” አልሁ።
13 “ ‘እንዲበላ የተፈቀደውን ማንኛውንም እንስሳ ወይም ወፍ አድኖ የያዘ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደሙን ከውስጡ ያፍስስ፤ ዐፈርም ያልብሰው፤
14 የማንኛውም ፍጡር ሕይወት ደሙ ነውና። ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “የፍጡር ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የማንኛውንም ፍጡር ደም አትብሉ፤ የበላው ሰው ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ” አልኋቸው።
15 “ ‘ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን የበላ ማንኛውም የአገር ተወላጅ ወይም መጻተኛ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።
16 ልብሱን ባያጥብ፣ ሰውነቱንም ባይታጠብ ግን ኀጢአት ሠርቶአልና ይጠየቅበታል።’ ”