19 ከወይፈኑም ሥቡን ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤
20 ለኀጢአት መሥዋዕት ባቀረበው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህኛውም ወይፈን ያድርግ፤ በዚህም መሠረት ካህኑ ስለ ሕዝቡ ያስተሰረያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ።
21 ወይፈኑንም ከሰፈር ውጭ ያውጣው፤ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይህኛውንም ያቃጥል፤ ይህም ስለ ሕዝቡ የሚቀርብ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።
22 “ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዛት አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው።
23 ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።
24 እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው።
25 ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍሰው።