5 እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቆሙ።
6 ሙሴም፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ፣ እንድታደርጉት እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዛችሁ ይህ ነው” አለ።
7 ሙሴ አሮንን፣ ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተሰርይ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተሰርይላቸውም” አለው።
8 አሮንም ወደ መሠዊያው መጥቶ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት የቀረበውን እምቦሳ ዐረደው።
9 ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ግርጌ አፈሰሰው።
10 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት የኀጢአት መሥዋዕቱን ሥብ፣ ኵላሊቶቹንና የጒበቱን ሽፋን በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤
11 ሥጋውንና ቊርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው።