1 በለዓም፣ “እዚህ ሰባት መሠዊያ ሥራልኝ፤ ሰባት ኮርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው።
2 ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ ሁለቱም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።
3 ከዚያም በለዓም ባላቅን፣ “እኔ ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ፤ ምናልባትም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው። ከዚያም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኰረብታ ሄደ።
4 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተገናኘው፤ በለዓምም፣ “እነሆ፤ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጅቻለሁ፤ በእያንዳንዱም ላይ አንድ ኮርማና አንድ አውራ በግ አቅርቤአለሁ” አለው።
5 እግዚአብሔርም (ያህዌ) በበለዓም አፍ መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመልሰህ ይህን መልእክት ንገረው” አለው።