ዘፀአት 7 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ልብ በል፤ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ (ኤሎሂም) አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህ አሮንም ያንተ ነቢይ ይሆናል።

2 እኔ የማዝህን ሁሉ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም እስራኤላውያንን ከአገሩ እንዲወጡ ይለቃቸው ዘንድ ለፈርዖን ይነግረዋል።

3 እኔ ግን የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፤ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በግብፅ ላይ በብዛት ባደርግም እንኳ፣ አይሰማችሁም።

4 ከዚያም እጄን በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፤ በኀያል ፍርድም ሰራዊቴን፣ ሕዝቤን እስራኤላውያንን አወጣለሁ፤

5 እጄን በግብፅ ላይ ስዘረጋና እስራኤላውያንንም ከዚያ ሳወጣ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ።”

6 ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ።

7 ፈርዖንን ባነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት፣ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ነበር።

የአሮን በትር እባብ ሆነች

8 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣

9 “ፈርዖን፣ ‘ታምር አሳዩኝ’ ባላችሁ ጊዜ፣ አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን ውሰድና በፈርዖን ፊት ጣላት፤’ ከዚያም እባብ ትሆናለች።”

10 ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮን በትሩን በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት ጣላት፤ እባብም ሆነች።

11 ከዚያም ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ የግብፅ አስማተኞችም በድብቅ ጥበባቸው ያንኑ አደረጉ፤

12 እያንዳንዱ የያዛትን በትር ጣለ፤ እባብም ሆነች። ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ዋጠች።

13 ሆኖም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተናግሮ እንደ ነበረውም አላዳመጣቸውም።

የደም መቅሠፍት

14 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም።

15 ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ።

16 ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው፤” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ እሺ አላልህም።

17 እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ በዚህች በእጄ በያዝኳት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ። ወደ ደምም ይለወጣል።

18 በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።’ ”

19 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብፅ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኩሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብፅ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።”

20 ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በንጉሡና በሹማምንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ። ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ።

21 በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብፃውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብፅ ምድር ሁሉ ደም ነበረ።

22 የግብፅ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።

23 ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህንን ከቍም ነገር አልቈጠረውም።

24 ግብፃውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጒድጓድ ቈፈሩ።

25 እግዚአብሔር (ያህዌ) አባይን ከመታ ሰባት ቀን አለፈ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40