12 ከዚያም ዳዊት፣ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮን በዚያ ዕለትና በማግስቱ እዚያው ኢየሩሳሌም ቈየ።
13 በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮን በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አሽከሮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም።
14 ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፤
15 በደብዳቤውም ላይ፣ “ኦርዮ ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ።
16 ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፣ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮን መደበው።
17 የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሰራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።
18 ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ።