2 ሳሙኤል

ምዕራፎች 11:18-24

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

18ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ። 19መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፣ 20ንጉሡ በቍጣ ቱግ ብሎ ‘ለመዋጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለምንድን ነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል? 21የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ቢጠይቅህ፣ አንተም መልሰህ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቶአል’ ብለህ ንገረው።” 22ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደ ደረሰም፣ ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው። 23መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳደን መለስናቸው። 24ከዚያም ባለ ፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፣ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።”