19 መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፣
20 ንጉሡ በቍጣ ቱግ ብሎ ‘ለመዋጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለምንድን ነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል?
21 የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ቢጠይቅህ፣ አንተም መልሰህ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቶአል’ ብለህ ንገረው።”
22 ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደ ደረሰም፣ ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው።
23 መልእክተኛውም ለዳዊት እንዲህ አለው፤ “ሰዎቹ አየሉብን፤ እኛንም ለመውጋት ወጥተው እስከ ሜዳው ድረስ መጡ፤ እኛ ግን እስከ ከተማዪቱ ቅጽር መግቢያ ድረስ አሳደን መለስናቸው።
24 ከዚያም ባለ ፍላጻዎቹ ከግንቡ ላይ ሆነው በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ ቀስት ስለ ለቀቁ፣ ከንጉሡ አገልጋዮች ጥቂቶቹን ገደሉ፤ አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።”
25 ዳዊትም፣ መልእክተኛውን፣ “እንግዲህ እንዲህ ብለህ ይህን ለኢዮአብ ንገረው፤ ‘መቼም ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን፣ ሌላ ጊዜም ሌላውን ትበላለችና በዚህ አትዘን” ’ አለው።