2 ሳሙኤል 14:18-24 NASV

18 ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፣ “እኔም ለምጠይቅሽ ነገር አንቺም መልሱን አትደብቂኝ” አላት።ሴቲቱም፣ “ንጉሥ ጌታዬ፤ እሺ ይናገር” አለችው።

19 ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት።ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። አዎን ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አንደበት እንዲነገር የላከኝ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው።

20 አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።”

21 ንጉሡም ኢዮአብን፣ “መልካም ነው፤ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።

22 ኢዮአብም አክብሮቱን ለንጉሡ ለመግለጥ ወደ መሬት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባረከ፣ ኢዮአብም በመቀጠል፣ “ንጉሡ የአገልጋዩን ልመና ስለ ተቀበለው፣ ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቱን ዛሬ ለማወቅ ችሎአል” አለ።

23 ከዚያም ኢዮአብ ወደ ጌሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው።

24 ንጉሡ ግን፣ “እዚያው እቤቱ ይሂድ፤ ዐይኔን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።