2 ሳሙኤል 14:6-12 NASV

6 እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው።

7 እነሆ ቤተ ዘመዱ ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፣ ‘ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለንና ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፣ ከዚያም ወራሽ አልባ ትሆኛለሽ’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።”

8 ንጉሡም ሴቲቱን፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ስለ ጒዳይሽ አስፈላጊውን ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት።

9 ነገር ግን የቴቁሔዪቱም ሴት፣ “ንጉሥ ጌታዬ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች።

10 ንጉሡም፣ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አያስቸግርሽም” ሲል መለሰላት።

11 እርሷም፣ “ደም ተበቃዮቹ ልጄን በማጥፋት የባሰ ጒዳት እንዳያደርሱ፣ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ይለምን” አለች።ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ጠጒር እንኳ አትነካም” አላት።

12 ከዚያም ሴቲቱ፣ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፣ “እሺ ተናገሪ” አላት።