1 ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ አምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ።
2 አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆን ብሎ ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጒዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል።
3 ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጒዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል።
4 ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር።
5 እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር።