2 ሳሙኤል 15:17-23 NASV

17 ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ።

18 ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ።

19 ንጉሡም ጌታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤

20 የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው።

21 ኢታይን ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል” ብሎ መለሰለት።

22 ዳዊትም ኢታይን፣ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይን ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ።

23 ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው ተጓዘ።