7 ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤
8 እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።”
9 ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ።
10 ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ።
11 ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በስተቀር፣ ስለ ጒዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም።
12 አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ።
13 መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው።