2 ሳሙኤል 18:1-7 NASV

1 ዳዊት አብሮት የነበረውን ሕዝብ ቈጠረ፤ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችን ሾመላቸው።

2 ዳዊትም ሰራዊቱን ሲሦውን በኢዮአብ፣ ሲሦውን በኢዮአብ ወንድም በጽሩያ ልጅ በአቢሳ፣ ሲሦውን ደግሞ በጌታዊው በኢታይ አዛዥነት ሥር ላካቸው። ንጉሡም ለሰራዊቱ፣ “እኔ ራሴም አብሬአችሁ በእርግጥ እወጣለሁ” አላቸው።

3 ሰዎቹ ግን፣ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፣ ሰዎቹ ከቁም ነገር አይቈጥሩንም፤ ግማሾቻችን እንኳ ብንሞት ደንታቸው አይደለም፣ አንተ ግን ብቻህን ከእኛ ከዐሥሩ ሺህ ትበልጣለህ፤ ስለዚህ በከተማ ሆነህ ብትረዳን ይሻላል” አሉት።

4 ንጉሡም፣ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ በመቶና በሺህ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ፣ ንጉሡ በቅጥሩ በር ቆሞ ነበር።

5 ንጉሡም ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ ልጄ በአቤሴሎም ላይ ጒዳት እንዳታደርሱበት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡ ልጁን አቤሴሎምን አስመልክቶ ለእያንዳንዱ አዛዥ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰራዊቱ ሁሉ ሰማ።

6 ሰራዊቱ እስራኤልን ለመውጋት ተሰልፎ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ጦርነቱም በኤፍሬም ደን ውስጥ ሆነ።

7 እዚያም የእስራኤል ሰራዊት በዳዊት ሰዎች ተመታ፤ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ሃያ ሺህም ሰው ተገደለ።