2 ሳሙኤል 18:24-30 NASV

24 ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ሳለ፣ ጠባቂው ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጥቶ ወደ ውጭ ሲመለከት አንድ ሰው ብቻውን ሲሮጥ አየ።

25 ጠባቂውም ተጣራና ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤ንጉሡም፣ “ብቻውን ከሆነ መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። ሰውየውም እየቀረበ መጣ።

26 ከዚያም ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ አይቶ፣ ዘበኛውን ተጣራና፣ “እነሆ ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለ።ንጉሡም፣ “ይኸኛውም መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ።

27 ጠባቂውም፣ “የመጀመሪያው ሰው ሩጫ የሳዶቅን ልጅ የአኪማአስን ሩጫ ይመስለኛል” አለ።ንጉሡም፣ “እርሱማ ጥሩ ሰው ነው፤ የምሥራች ሳይዝ አይመጣም” አለ።

28 አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን፣ “ሁሉም ነገር ተሳክቶአል” አለ፤ ከዚያም ወደ መሬት ለጥ ብሎ በንጉሡ ፊት እጅ ነሣና፣ “በጌታዬ በንጉሡ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!” አለ።

29 ንጉሡም፣ “ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን?” ሲል ጠየቀ።አኪማአስም፣ “ኢዮአብ የንጉሡን አገልጋይና እኔንም ባሪያህን ሊልክ ሲል፣ ትልቅ ሁካታ አይቻለሁ፤ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም” ብሎ መለሰ።

30 ንጉሡም፣ “እልፍ በልና ቁም” አለው፤ ስለዚህ እልፍ ብሎ ቆመ።