35 እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ ደግና ክፉውን መለየት እችላለሁ? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንም መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል?
36 አገልጋይህ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከንጉሡ ጋር ጥቂት መንገድ ይሄዳል፤ ነገር ግን ንጉሡ በዚህ ሁኔታ ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው?
37 በገዛ ከተማዬ ሞቼ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እቀበር ዘንድ፣ አገልጋይህን አሰናብተውና ይመለስ፤ ነገር ግን አገልጋይህ ከመዓም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት።”
38 ንጉሡም፣ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገራል፤ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ከእኔ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለአንተም አደርግልሃለሁ” አለው።
39 ስለዚህም ሕዝቡ በሙሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ከዚያ በኋላም ንጉሡ ተሻገረ። ንጉሡ ቤርዜሊን ስሞ መረቀው፤ ቤርዜሊም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
40 ንጉሡ ወደ ጌልጌላ ሲሄድ፣ ከመዓም አብሮት ሄደ። የይሁዳ ሰራዊት በሙሉ እንዲሁም ግማሹ የእስራኤል ሰራዊት ንጉሡን አጅበው አሻገሩት።
41 ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው፣ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን በሹልክታ ለብቻቸው ይዘው እርሱንና ቤተ ሰውን ከተከታዮቹ ጋር ዮርዳኖስን ለምን አሻገሩ?” አሉት።