2 ሳሙኤል 19:8-14 NASV

8 ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጦአል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ።በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደ የቤታቸው ሸሽተው ነበር።

9 በመላው የእስራኤል ነገዶችም፣ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዶአል፤

10 በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቶአል፤ ታዲያ ንጉሡን የመመለሱን ጒዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?”

11 ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለ ሆነ፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?

12 እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’

13 አሜሳ ይንም፣ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሰራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፣ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።”

14 እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም ሰዎችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት።